Saturday, April 30, 2016

እንኳን ለጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የትንሳኤ በዓል በሰላም አደረሰን፥ አደረሳችሁ!

እንኳን ለጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የትንሳኤ በዓል በሰላም አደረሰን አደረሳችሁ!


በዐማርኛችን ፋሲካ የምንለው ቃል በዕብራጥስጥ አፍ፥ አቻ ቃሉ פֶּסַח 6453 pecach peh'-sakh፣ ፔሳኽ” የሚል ሲሆን ትርጓሜውም “አለፈ፣ ተሻገር” እንደማለት ነው። ይህ ፋሲካ የሚለው ቃል የዐማርኛ ቃል ትርጓሜው፥ ፍሥሃ፣ ሐሴት፣ መሻገር፣ ማለፍ ማለት ነው፡፡

 ከዚህ በመነሳት በዓለ ፋሲካ የምናከብረው፥ በጌታችንና በመድኃኒታችን በኢየሱስ ክርስቶስ ደም ሞትን ተሻግረን፣ ባርነትን አምልጠን፣ የእግዚአብሔር ልጆች የሆነበትን የትንሳኤውን ድል በማስብ ነው፡፡ ይህ በዓል በመጽሐፍ ቅዱሳችን ላይ በዘጽአት መጽሐፍ፥ በአሥራ ሁለተኛው ምዕራፍ ላይ ከሰፈረው ታሪክ ጥላነቱን ይዞ የሚጀምር ነው፥

·        እኔም በዚያች ሌሊት በግብፅ አገር አልፋለሁ፥ በግብፅም አገር ከሰው እስከ እንስሳ ድረስ በኵርን ሁሉ እገድላለሁ በግብፅም አማልክት ሁሉ ላይ እፈርድባቸዋለሁ እኔ እግዚአብሔር ነኝ። ደሙም ባላችሁበት ቤቶች ምልክት ይሆንላችኋል ደሙንም ባየሁ ጊዜ ከእናንተ አልፋለሁ እኔም የግብፅን አገር በመታሁ ጊዜ መቅሰፍቱ ለጥፋት አይመጣባችሁም። ዘጽ 12፥12-13፡፡

ጌታ እግዚአብሔር እስራኤላውያንን ባዘዛቸው መሰረት፥ ከአንድ ዓመት የማይበልጠውን የፍየል ወይም የበግ ጠቦት መስዋዕት አርደው፥ የቤታቸውን መቃንና ጉበን ከመስዋዕቱ ደም ቀብተው፥ ያልፍ ከነበረው የእግዚአብሔር መቅሰፍት አምልጠዋል፡፡ የእግዚአብሔር መቅሰፍት በመጣ ጊዜ፥ የደሙ ምልክት የሌለውን ቤት እየገባ በኩረ ግብጽን በሞት ሲቀጣ፥ እስራኤላውያንን ግን ይህ ታላቅ መቅሰፈት ቤታቸውን እንኳ ሳያንኳኳ፥ በመቃኑና በጉበኑ ላይ ከተቀባው የመስዋዕቱ ደም የተነሳ ያልፍ ነበር፡፡ ይህም ፋሲካ ተባለ።

ይህ ሁሉ ለአዲስ ኪዳኑ ፋሲካ፥ ጥላ ሆኖ የቆየ ነበር፡፡ አካላዊው ፋሲካ ጌታችን ኢየሱስ መሆኑን የአዲስ ኪዳን ቅዱሳት መጻሕፍት ይመሰክራሉ፥

·        «እንግዲህ ያለ እርሾ እንዳላችሁ አዲሱን ሊጥ ትሆኑ ዘንድ አሮጌውን እርሾ አስወግዱ። ፋሲካችን ክርስቶስ ታርዶአልና» 1ኛ ቆሮ 5፥7።  

በአዲስ ኪዳን ደግሞ ከሞት የሚያስመልጥ የደሙ ምልክት ኢየሱስ ክርስቶስ ነው። ይህ መስዋዕት ሰው ያላዘጋጀውና በራሱ በእግዚአብሔር ለሰው ልጆች ከሞት የመዳን ዋስትና የተዘጋጀ ሲሆን እንደ ብሉይ ኪዳኑ መስዋዕት በየጊዜው ደም በማፍሰስ ከሞት ለማዳን ያልቀረበ ነገር ግን አንዴ ተፈጽሞ ለዘለዓለሙ የሚያገለግል ዘላለማዊ የመስዋዕት ደም ነው። ለዛም ነው ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ፥ የቀደመው ማንነታችንን ትተን፥ የዐመጻና የኃጢአት እርሾችንን በንስሐ አስወግደን፥ በእምነት የምንቀበለው አዲሱ ፋሲካ ክርስቶስ እንደሆነ የጻፈልን። ይህም ብቻ አይደለም፥ እስራኤላውያንን የፍየል መስዋዕቱ ደም ያልፍ ከነበረው ከቁጣው መቅሰፍት እንዳሻገራቸው ሁሉ፥ የአዲስ ኪዳኑ ነውርና ነቀፋ የሌለው የጌታችን የኢየሱስ ደም ደግሞ ከዘላለም ሞት ብቻ ሳይሆን የእግዚአብሔር ልጅ የመሆንን ጸጋና ርስቱንም ጨምሮ አውርሶናል፥

·        “ስለዚህም የፊተኛው ኪዳን ሲጸና ሕግን የተላለፉትን የሚቤዥ ሞት ስለ ሆነ፥ የተጠሩት የዘላለምን ርስት የተስፋ ቃል እንዲቀበሉ እርሱ የአዲስ ኪዳን መካከለኛ ነው።” ዕብ 9፥15፡፡

አሜን!! መልካም የትንሳኤ በዓል ይሁንል!!

Tuesday, April 26, 2016

ሰው እናታችን ጽዮን ይላል!

ክፍል ሁለት
በዲያቆን ይስማዕከ ይነግስ
       
          እናት ኦርቶዶክሳዊት ተዋህዶ ቤተክርስቲያናችን ከመሰረቷ አንስታ እስከ ጉልላቷ፥ ክብሯና ማዕረጓ፥ የማምለጫ አለቷ፥ የጌቶቹ ሁሉ ጌታ መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ነው፡፡ በመልካሙ አዝማራ መሐል እንክርዳድ አይጠፋምና አንዳንድ ለሆዳቸው ያደሩ እኩያነ መናፍቃን እንግዳ አስተምህሮ በቤተክርስቲያናችን ውስጥ ሲያስተምሩ ይደመጣል፡፡ ለስህተት ትምህርታቸው ዐውደ ምንባቡንና ጥቅል የቃለ እግዚአብሔርን አስተምህሮ ማዕከል ሳያደርጉ እንዲሁ ቃል ይጠቅሳሉ፥


·        ሰው እናታችን ጽዮን ይላል፥ በውስጥዋም ሰው ተወለደ እርሱ ራሱም ልዑል መሠረታት። እግዚአብሔር ለሕዝቡ፥ በውስጥዋም ለተወለዱት አለቆችዋ በመጽሐፍ ይነግራቸዋል። በአንቺ የሚኖሩ ሁሉ ደስ እንደሚላቸው ይነግራቸዋል።” መዝ 86(87)፥5-7፡፡
·         
        በዚህ ክፍል እናታችን ጽዮን የተባለችው ቅድስት ድንግል ማርያም ናት በማለት ይናገራሉ፡፡ እኛም በበኩላች ቅድስት ቤተክርስቲያን እንዳስተማረችን እንዲህ እንላለን፡-

1.      በመጀመርያ ይህን የምስጋና መዝሙር የተቀኙት የቆሬ ልጆች እንጂ ዳዊት አይደለም (የምዕራፉን ርዕስ ይመልከቱ)፡፡ ሲቀጥል ቁጥር 1 ላይ መሠረቶቹ በተቀደሱ ተራሮች ናቸው እንደሚል ዝማሬው፥ በወንድ አንቀጽ ሲጠራ እንጂ መሰረቶቿ የሚል ቃልን አናነብም፡፡ አንዳንድ ግለሰቦች በስብከታቸውና በመጽሐፋቸው ላይ ሲዘግቡ ግን መሰረቶቿ በተቀደሱ ተራሮች ነው በማለት ለድንግል ማርያም አላግባብ በመቀጸል ለሚለፉት ልፈፋ ተሐቅቦ ይሆንላቸው ዘንድ እንደቃሉ እንመክራለን፡፡

2.     አስቀጥሎም በዝማሬው ቁጥር ከ2-3 ላይ “ከያዕቆብ ድንኳኖች ይልቅ፥ እግዚአብሔር የጽዮንን ደጆች ይወድዳቸዋል። የእግዚአብሔር ከተማ ሆይ፥ በአንቺ የተከበረ ነገር ይባላል።” እንደሚል ዝማሬው የጽዮን ደጆች ብዛት ያላቸው መሆናቸው ስለሚነግረን ድንግል ማርያም ናት ማለት ክህደት ይሆናል፡፡ ብዛት ያለው ደጅ የሚገባው ለሐገር አልያም ለከተማ እንጂ ለተወደደችው ለቅድስት ድንግል ማርያም አይደለም፡፡ ድንግል ማርያም ብዙ ደጆች አሏት ብሎ ባለማስተዋልም ቢሆን እንደ ማህበረ ቅዱሳን መስበክ፥ ስድብ ካልሆነ በቀር እውነታነት የለውም፡፡ ለዛም ነው፥ የእግዚአብሔር ከተማ በመባል ብዛት ባለው ደጆች የተገለጠችው፡፡ ይህችው የእግዚአብሔር ከተማ፥ በክፍሉ እንደምንመለከተው ጽዮን በሚል ስያሜ ነው የተጠራችው፡፡ ዐውደ ምንባቡ የእግዚአብሔር ከተማ ስለተባለችው ጽዮን እንጂ ስለ ድንግል ማርያም የሚያወራ አይደለም የሚያስጠርጥርም ነገር አይናገርም፡፡

3.     ቁጥር 5 እንዲህ ይነበባል፡- ሰው እናታችን ጽዮን ይላል፥ በውስጥዋም ሰው ተወለደ እርሱ ራሱም ልዑል መሠረታት፡፡” በዚህ ዝማሬ ላይ የእግዚአብሔር ከተማ የተባለችው፣ ብዛት ያለው ልጆች ያሏት የጽዮን ከተማ፣ በውስጧ ሰው እንደተወለደ፣ ከዚህም የተነሳ እናት ልትባል እንደቻለች ይነግረናል፡፡ በዚህ ምንባብ ሁሉም ሰው ሊያስተውል የሚገባው በውስጥዋም ሰው ተወለደ እንጂ ከእርሷም ሰው ተወለደ ተብሎ አለመጻፉን ይሆናል፡፡ ይህም የሚያሳየን ከተማይቱ ጽዮን በውስጧ ሰው ተወለደ የተባለችው ሐገር በመሆኗ እንደሆነ የተገለጠ ነው፡፡ ከዚህ በተረፈ እንደ ደባትራኑ የበሬ ወለደ ቅዠት ካለፈፍን በቀር በሰው ማህጸን ውስጥ ሰው ሊጸነስ እንጂ ሊወለድ ከቶ እንደማይችልበሁሉ ዘንድ የታወቀ ነው፡፡ በሰው ውስጥ ሰው ተወለደ ብሎ መስበክ 21ኛው ክፍለ ዘመንን የማይመጥን ተራ ተረት ይሆንብናል፡፡

4.     በተጨማሪም በዚህ ክፍል ሰው እናታችን ጽዮን ይላል” እንደሚል ቃሉ እናታችን እንጂ እናቱ አለማለቱን ልብ ይሏል፡፡ ይህም የሚያሳየን በጽዮን ከተማ ውስጥ የተወለዱት ሰዎች ብዛት ያለቸው በመሆናቸው ምክንያት //እናታችን// እያሉ ሊጠሯት መቻላቸውን ነው፡፡ ከዚህ በተለየ ሁኔታ ግን ጽዮን የተባለችው የእግዚአብሔር ከተማ አንድ ልጅ ብቻ መውለዷን ዝማሬው አያስተምረንም፡፡

5.     ይቀጥልና ቁጥር 6 ላይ በተመሳሳይ መልኩ “በውስጥዋም ለተወለዱት አለቆችዋ በመጽሐፍ ይነግራቸዋል።” በማለት ከጽዮን የተወለዱት በቁጥር ያልተገለጡ ነገር ግን ብዙ ሰዎች መሆናቸው ይነግረናል፡፡ ብዛት ያላቸው የጽዮን ልጆች እናታችን እያሉ እንደሚጠሯት እንጂ ጽዮን አንድ ልጅ ብቻ ስለመውለዷ ክፍሉ አይናገርም፡፡ እነዚህ ብዛት ያላቸው የጽዮን ልጆች “በውስጥዋም ለተወለዱት አለቆችዋ እንደሚል ቃሉ መልሰው በራሷ በጽዮን ላይ አለቆች እንደሆኑ ይነግረናል፡፡ እንግዲህ ይህን ግልጽ የዝማሬ መልዕክት በምን በኩል ቢሰላ ነው ለድንግል ማርያም ልንቀጽለው የሚገባን? እንዲሁ ድንግል ማርያምን ከፍ ያደረግናት እየመሰለን፥ መንፈስ ቅዱስ የማይከብርበትን የሰዎች ፍልስፍና በማስተጋባት፥ ቃሉ የማያስተምረውን በመንዛት፥ በማወቅም ይሁን ባለማወቅ ድንግልን እያጥላላን መሆኑን ልብ ልንል ይገባል፡፡

6.   በዝማሬው የመጨረሻ ቁጥር እንዲህ ተብሎ ተደምድሟል፡- “በአንቺ የሚኖሩ ሁሉ ደስ እንደሚላቸው ይነግራቸዋል።” በማለት ጽዮን የሰዎች መኗሪያ ከተማ እንደሆነች በግላጭ ያስረዳናል፡፡ ጽዮን የመኖሪያ ከተማ ከመሆኗም ባሻገር በአንቺ የሚኖሩ በማለት በጽዮን ውስጥ የሚኖሩ እጅግ በርካታ ሰዎች መሆናቸውን ይነግረናል፡፡ ከዚህ በተረፈ ድንግል ማርያም ክርስቶስን ለ 9 ወር በማህጸኗ እንደተሸከመች እንጂ በማህጸኗ ውስጥ ክርስቶስ መኗሪያውን አበጅቶ እንደነበር ሁሉ ቤተክርስቲያን አላስተማረችንም፡፡


እንግዲህ ቃሉንና ቤተክርስቲያንን እናድምጥ ወይስ የደብተራዎችን ቅዠት እናድምጥ?

... ይቀጥላል ...

Saturday, April 23, 2016

ሆሣዕና በአርያም! ለዳዊት ልጅ! ሃሌሉያ!

  
እንኳን ለሆሣዕና በዓል አደረሰን! አደረሳችሁ!

“ሆሣዕና” የሚለው ቃል ከአሮማይክ ሁለት ቃላት የተጣመረ ሲሆን ትርጓሜውም አሁን አድን የሚል ነው፡፡ የዕብራይስጡ “ሆሻአና” የሚለው ቃል ከአሮማይኩ ቃል የተገኘ ሲሆን፥ ጥንታዊ የቅዱሳት መጻሕፍት ጥናትהֹושִׁ֘יעָ֥ה, 3467 hō-wō-šî-‘āh ሆሻአና” በማለት ያስቀምጠዋል፡፡ ይህንኑ ቃል በመዝሙር መጽሐፍ ቅዱስ ዳዊት አስቀድሞ በትንቢት መንፈስ “ሆሣዕና” በማለት ጌታችን ኢየሱስ ማዳኑን እንዲያፈጥን ሲማጸነው እንመለከታለን፥

·        “አቤቱ፥ እባክህ፥ አሁን አድን አቤቱ፥ እባክህ፥ አሁን አቅና፡፡ Save now, I beseech thee, O Lord: O Lord, I beseech thee, send now prosperity. אָנָּ֣א יְ֭הוָה הֹושִׁ֘יעָ֥ה נָּ֑א אָֽנָּ֥א יְ֝הוָ֗ה הַצְלִ֘יחָ֥ה נָּֽא׃መዝ ፻፲፰፥፳፭ ፡፡ (በነገራችን ላይ በዚህ ክፍል ንጉስ ዳዊት ያህዌ  יְ֭הוָה, Yah-weh በማለት ሲማጽን የምንመለከተው ጌታችን ኢየሱስን ነው፡፡ ይህም ጌታችን ኢየሱስ ሁሉን ቻይ አምላክ፣ ያለና የነበረ ደግሞም የሚኖር፣ ያህዌ መሆኑን የሚያስረዳ ነው፡፡)

አባቶች በመንፈስ ቅዱስ ምሪት አዳኝ ስለሆነው መሲህ በቅዱሳት መጻሕፍት ዘገባ መሰረት፥ አብዝተው ትንቢትን የተናገሩለት ሲሆን ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ያድናቸው ዘንድ፥ በውርጭላ ላይ ተቀምጦ ከደብረ ዘይተና ከቤተ ፋጌ ወደ ቤተልሔም እንደሚመጣ፥ ነብዩ ዘካርያ በትንቢት መጽሐፉ ላይ እንዲህ ሲል አስፍሯል፥

·        አንቺ የጽዮን ልጅ ሆይ፥ እጅግ ደስ ይበልሽ አንቺ የኢየሩሳሌም ልጅ ሆይ፥ እልል በዪ እነሆ፥ ንጉሥሽ ጻድቅና አዳኝ ነው ትሑትም ሆኖ በአህያም፥ በአህያይቱ ግልገል በውርጫይቱ ላይ ተቀምጦ ወደ አንቺ ይመጣል ዘካ ፱፥፱፡፡

ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስም አባቶች በትንቢት እንደተናገሩለት፥ የዘመኑ ፍጻሜ፥ ሰዓቱ በደረሰ ጊዜ፥ እባክህ አሁን አድን እያሉ የለመኑትን ቃል ሰምቶ፥ ከቅድስት ድንግል ማርያም ያለዘርዓ ብእሲ ሥጋ ሆኖ በመወለድ፥ የዓለምን ኃጢአት በስጋው ተሸክሞ ወደ እግዚአብሔር መንግስት አፍልሶናል፡፡ በመጽሐፍ እንደተነገረለት በአህያይቱ ውርጭላ ላይ ጌታችን ተቀምጦ ወደ ቤተልሔም በገባ ጊዜ ከሕጻን እስከ አዛውንቱ ድረስ ልብሳቸውንም አንጥፈው ተቀበለውታል፥ የዘንባባ ዝንጣፊውንም በእጃቸው ጨብጠው ለክብሩ ተቀኝተውለታል፥ እንዲህም እያሉ በአንድነት ይዘምሩለት ነበር፥

·        የሚቀድሙትም ሕዝብ የሚከተሉትም። ሆሣዕና ለዳዊት ልጅ በጌታ ስም የሚመጣ የተባረከ ነው፤ ሆሣዕና በአርያም እያሉ ይጮኹ ነበር ማቴ ፳፩፥፱፡፡ አሜን! አሜን! ሆሣዕና በአርያም! ለዳዊት ልጅ ለጌታችን ኢየሱስ! ሃሌሉያ!

የሚገርመው ግን የካህናት አለቆች፥ በመጻሕፍት የተነገሩት በሙሉ እየተፈጸሙ መሆኑን ተመልክተው፥ ልባቸውን ወደ እግዚአብሔር ልጅ፥ ወደ እውነተኛው መሲሕ፥ ወደ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ከማዘንበል ይልቅ ክፍትን በልባቸው ተሞልተው ይቃወሙት ነበር፡፡ ዛሬስ ስንቶቻችን እንሆን ስለ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በተሰበከ ጊዜ፥ ቅዱስ ስሙ በዝማሬ በተመሰገነ ጊዜ ልባችን የሚከፋው? ስንቱንስ ከእናት ቤተ ክርስቲያን መናፍቅ፥ ጴንጤ እያልን ገፍተን አባረርነው? በእውነት፥ ምህረትና ቸርነቱ ይብዛልን! አይሁድ ጌታችንን ከማክበር ይልቅ ልባቸውን በሐሰት ክስ ሞልተው፥ የሠራቸውን ተአምራት ተመልክተው፥ ሕዝቡም ሁሉ በዝማሬ ሲያመሰግኑት አይተው፥ ይገዳደሩት ዘንድ በቅንዓት ተነሱበት እንዲህ ሲሉ፥

·        «ነገር ግን የካህናት አለቆችና ጻፎች ያደረገውን ድንቃ ድንቅ በመቅደስም፣ ሆሣዕና ለዳዊት ልጅ እያሉ የሚጮኹትን ልጆች ባዩ ጊዜ፥ ተቈጥተው፣ እነዚህ የሚሉትን አትሰማምን? አሉት» ማቴ ፳፩፣ ፲፭፡፡

ጌታችንና መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስም “እውነት ብላችኋል፥ ለእኔ ዝማሬ አይገባም” አላላቸውም፥ ይልቁንም የቅዱሳት መጻሕፍትን የትንቢት ቃል ነበር ማስረጃ አድርጎ በማቅረብ (ከሕፃናትና ከሚጠቡ ልጆች አፍ ምስጋናን አዘጋጀህ መዝ ፥፪) ምስጋና የተገባው እውነተኛ ጌታና አምላክ መሆኑን እንዲህ ሲል ነበር ያረጋገጠላቸው፥  
·        «እሰማለሁ፤ ከሕፃናትና ከሚጠቡት አፍ ምስጋናን ለራስህ አዘጋጀህ የሚለውን ቃል ከቶ አላነበባችሁምን? አላቸው»  ማቴ ፳፩፥፲፮፡፡

በእውነት ጌታችን ኢየሱስ አድኖናል፥ ቤዛ ሆኖ ነፍሳንን ከዘለዓለም ሞት አድኗታል፥ በትንቢት እንደተነገረለት ሕዝቡን ሁሉ ከኃጢአት ለማዳን ሲል ራሱን መስዋዕት አድርጎል፥ ይኽውም እስከ መስቀል ሞት የታመነ ሆኗል፥ ስለ እኛም በደል ርግማን ሆኖ ከሕግ ርግምን ዋጅቶናል፥ እንደሞተም አልቀረም በክብር ሞትን ድል ነስቷል፥ በኃይልና በልዕልና ወደ ሰማያት ከፍታ በማረግ በአባቱ ቀኝ በክብር ተቀምጧል፡፡ ደግሞም ወደ አባቱ ሊወስድን ተመልሶ ይመጣል! ክብር ይግባው!!

አሜን! ሆሣዕና በአርያም! ለዳዊት ልጅ ለጌታችን ኢየሱስ! ሃሌሉያ!   

Friday, April 22, 2016

ነገረ ጽዮን

ክፍል አንድ፥ 
በዲያቆን ይስማዕከ ይነግስ
        በዚህ ዘመን ቅድስት ቤተክርስቲያንን ከሚረብሹ እንግዳ አስተምህሮቶች መካከል አንዱ ጽዮን - ማርያም ናት የሚለው ኑፋቄ ነው፡፡ ይህን እንግዳ ትምህርት ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በነገረ መለኮት ትምህርተ ዘለቀ እውቀት በሌላቸው በደባትራኑና ቤተክርስቲያኗን ለፖለቲካ አጀንዳቸው ሲሉ ሽፋን አድርገው በሕቡዕ በሚንቀሳቀሱ ግለሰቦች ዘንድ በስፋት ሲነገር ይደመጣል፡፡ ጽዮን - ማርያም ናት የሚለው ፍልስፍና ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ቀስ በቀስ የብዙዎችን ልቡና እያሳወረ፥ የስህተት አስተምህሮ ምርኮኛ ሊያደርጋቸው ችሏል፡፡ ቤተክርስቲያን ግን ለእኛ ልጆቿ በመጻህፍቶቿ ያላት አስተምህሮ ጽዮን - ማርያም ናት የሚል ፍልስፍና አይደለም፡፡ በማስረጃዎች እንመልከት፡-

1.     “እምነ ጽዮን በሐ ቅድስት ቤተክርስቲያን ሥርጉተ ስብሃት ... እንተ ክርስቶስ መሰረትኪ ጸሐየ ጽድቅ ያበርህ ለኪ፡፡” የአማርኛ ትርጓሜው እንዲህ ይላል፡- “ክርስቶስ የመሰረተሸ የጽድቅ ጸሐይ የሚያበራብሽ ምስጋናን የተሸለምሽ እናታችን ጽዮን ቅድስት ቤተክርስቲያን እንዴት ነሽ?” ምንጭ፡- (መጽሐፈ ዚቅ፣ ገጽ 73 ይመለከቷል)፡፡ በዚህ ክፍል የምንማረው ጽዮን - ማርያም ናት የሚል ሳይሆን፤ ይልቁንም በሐዋርያት አስተምህሮ፣ በአዲስ ኪዳን ቅዱሳት መጻሕፍት ምስክርነት መሰረት ጽዮን - ቤተክርስቲያን እንደሆነች ነው የሚነግረን፡፡ እንግዲህ ማንን እንስማ ዘንድ ይገባናል?

2.    “ዕዝራኒ ርእያ ለጽዮን ቅድስት እንዝ ትበኪ ከመ ብእሲት” የአማርኛ ትርጓሜው እንዲህ ይለናል፡- “ዕዝራም ጽዮን ቅድስትን እንደሴት ስታለቅስ አያት”  ምንጭ፡- (መጽሐፈ ዚቅ፣ ገጽ 72 ይመልከቱ)፡፡ በዚህ ምንባብም በተመሳሳይ መልኩ ጽዮንን *እንደ ሴት ስታለቅስ አየሁ* በማለት ጽዮን ስለተባለችዋ ኢየሩሳሌም በሰውኛ ዘይቤ፥ ከተማዋ ምን ያህል በሐዘን ድባብ መወረሷን፥ ካህኑ ዕዝራ ሲገልጻት እንመለከታለን፡፡ ከዚህ በተረፈ ጽዮን - ማርያም ናት የሚልን ፍልስፍና አናስተውልም፡፡

3.    “ዕዝራኒ ርእያ ለጽዮን ቅድስት በረእየተ ብእስት ወሶበ ርእያ ኢኮነት ብእስተ አላ ሀገር ቅድስት” የአማርኛ ትርጓሜው እንዲህ ይለናል፡- “ዕዝራም ጽዮን ቅድስትን በሴት አምሳል (መልክ) አየሁ፡፡ ባያት ጊዜም ሴት አይደለችም የተቀደሰች ሐገር ናት እንጂ፡፡” ምንጭ፡- (መጽሐፈ ዚቅ፣ ገጽ 73 ላይ ይመልከቱ)፡፡ በዚህ ምንባብ ካህኑ ጽዮን የተባለችዋን ኢየሩሳሌምን በሴት አምሳል ወይንም መልክ በራዕይ እንዳያት ይነግረናል እንጂ አካላዊ ሴትን አለማየቱን በግላጭ ያስረዳል፡፡ ይህም ብቻ አይደለም ኢኮነት ብእስቲ፥ ሴት አይደለችም በማለት የተመለከተው ሐገር መሆኑን ያስረግጣል እንጂ ፈጽሞ ዮን - ማርያም ናት የሚልን እንግዳ ኑፋቄ አይሰብከንም፡፡

4.   “አብርሂ አብርሂ ጽዮን ዕንቁ ዘጳዝዮን ዘኀረየኪ ሰሎሞን” የአማርኛ ትርጓሜው እንዲህ ይነበባል፡- “ሰሎሞን የመረጠሸ የጳዝዮን ዕንቁ አብሪ አብሪ፡፡” ምንጭ፡-(መጽሐፈ ዚቅ፣ ገጽ 73 ይመልከቱ)፡፡ ይህ ክፍል ከላይ እንደተመለከትነው ጽዮን ስለተባለችው ኢየሩሳሌም የሚተርክ ምንባብ ነው እንጂ እንዳችስ እንኳ ደባትራኑ እንደሚሉት ጽዮን ማርያም ናት የሚል አይደለም፡፡

እንግዲህ እኛ ቤተክርስቲያንን እንስማ ወይስ የሐሰት አስተማሪዎችን እንግዳ ኑፋቄ እናድምጥ? ለተጨማሪ መረጃ፡- ኪዳነ ምህረት መጽሄት፣ ቁጥር 18፣ በእንተ ጽዮን የሚለው ትምህርት ያንብቡ!


... ይቀጥላል ...

Thursday, April 21, 2016

ሰበር ዜና፥ ግልባጭ ለሐራ ዘተዋህዶ ብሎግ

        ዲያቆን ደቀመዝሙር ከፍያለው ቱፋ ‹‹መንፈሳዊ ጉባኤ አዘጋጅተህ፥ ሰዎችን ሰብሰበሃል›› በሚል ተቃውሞ ክስ ተመስርቶበት፥ ከሰሞኑ 18 ከሚደርሱ ቅዱሳን ጋር መታሰሩን ሐራ ዘተዋህዶ መዘገቧ የሚታወቅ ነው፡፡ አሁን በደረሰን መረጃ መሰረት ደቀመዝሙር ከፍያለው ቱፋ የተከሰሰበት ክስ ፍሬ ከርስኪ መሆኑን ተረድቶ፥ ትላንት ማለትም 12/08/2008 ዓ/ም በአንድ ሺህ ብር ዋስ ፍርድ ቤቱ ሊለቀው ችሏል፡፡ ፍርድ ቤቱም አክሎም የማንንም ሃይማኖት መስደብ፣ መንቀፍና መዝለፍ በሕግ ፈጽሞ የተከለከለ ነው፤ ደግሞም ማንም ሰው ያማነበትን እውነት መመስከርና መስበክ እንደሚችል ገልል፡፡ በቦታው ላይ ፖሊስ ደርሶ ነገሩን ባይቆጣጠር ኖሮ ደም በማፍሰስ የሚያምነው ማህበሩ፥ የወንድሞችንና የእህቶችን ደም ከማፍሰስ እንደማይቦዝን የታወቀ ነው፡፡ ኽረ ለመሆኑ ለሃይማኖት የተደባደበ ሐዋርያ ማን ነው?

         አሁን አሁን በእናት ቤተክርስቲያናችን ውስጥ ባሉ አንዳንድ ጽንፈኛ ግለሰቦች ምክንያት ወንድሞች በጋራ ተሰባስበው መጽሐፍ ቅዱስን ከተማማሩ፣ በአንድነትም በመዝሙር በቅኔ ለአምላካቸው ከተቀኙ እንደ ምንፍቅና መታየት ከተጀመረ ሰነባብቷል፡፡ ይሁንም እንጂ ቅድስት ቤተክርስቲያን፥ የጌታችንን የኢየሱስ ክርስቶስን ቀዳሚ ትምህርት መሰረት አድርጋ ወንጌል ለፍጥረት ሁሉ በየትኛውም ሥፍራ መሰበክ እንዳለበት ታስተምራለች፡-

·         እንግዲህ ሂዱና አሕዛብን ሁሉ በአብ በወልድና በመንፈስ ቅዱስ ስም እያጠመቃችኋቸው፥ ያዘዝኋችሁንም ሁሉ እንዲጠብቁ እያስተማራችኋቸው ደቀ መዛሙርት አድርጓቸው፡፡ ማቴ 28፡-19፡፡

         ደቀመዝሙሩና ከእርሱ ጋር የታሰሩ ወገኖች፥ ይሄንን የሐሰት ክስ ያቀነባበሩባቸውን ግለሰቦች መልሳችሁ መክሰስ ትችላላችሁ ቢባሉም እንኳ በቀል የእግዚአብሔር ነው በማለትና ከአባታችን ከእግዚአብሔር የተማርነው ይቅርታና ምህረት ማድረግ ነው በማለት አንዳችም አጸፋ ለማድረስ እንዳልፈለጉ ውስጥ አዋቂዎች ይናገራሉ፡፡ ይሄ ደግሞ የአሰበ ተፈሪ ሐገረ ስብከት ሠራተኞችን ትዝብት ውስጥ የሚጥልና በቤተክርስቲያንም ወንጌል ለምን ተማማራችሁ በማለት የሚያሳስርና የሚከስ አባት የላትም፡፡ ይህንን ያደረጉት የገባውን እውነት ቀብሮ ልጆቼን በምን አሳድጋለሁ ብሎ በግልጽ ወንጌልን የሚቃወመው  ላዕከ ወንጌል ምንዳ ጉታ፥ ትዳሩን ባለማክበር በምንዝርና የሚታወቀው ሊቀ ብርሃናት ካህሊ በቃሉ፥ እና የሴት አሳዳጁ በሚል ቅጽል ስም የሚጠራው መልአከ ጸሐይ ዮሐንስ ቀሲስ የማታ ወርቅ በተባሉ ግለሰቦች ሲሆኑ እነዚህ ሰዎች በዓመጻ ተነሳስተው ከማህበሩ በሚያገኙት የአልኮል ቅምሻ ተታለው መሆኑን ታውቋል፡፡



ወጥመድ ተሰበረ እኛም አመለጥን እንዲል መጽሐፍ ክብር ሁሉ ለእግዚአብሔር ብቻ ይሁን! አሜን!

Wednesday, April 20, 2016

ሁዳዴን ለጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ


እንኳን ለታላቁ የዐብይ (የሁዳዴ) ጾም በሰላም አደርሰን፣ አደረሳችሁ!

       እናት ኦርቶዶክሳዊት ተዋህዶ ቤተክርስቲያናችን ካሏት አጽዋማት መካከል አንዱና ዋነኛው //ዐቢይ ጾም ወይንም ሁዳዴ// የሚባለው ነው። «ሁዳዴ» የሚለውን ቃል የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን ከልደተ ክርስቶስ እስከ 2000ዓ/ም በሚለው በሊቃነ ጳጳሳቱ የተጻፈው መጽሐፍ በገጽ 32 ላይ እንዲህ ሲል ይፈታዋል፡- «ዐቢይ ጾም መባሉም የጌታ ጾም ስለሆነ ነው፣ ታላላቅ የሰይጣን ፈተናዎች (አርእስተ ኃጣውእ) ድል የተነሱበት፣ ድል የሚነሱበት ስለሆነ ነው፣ በሕዝቡም ዘንድ ሁዳዴ ይባላል። ሁዳዴ ማለት የመንግስት መሬት የመንግስት ርስት ማለት ነው።» ይለናል።

       በዚሁ **የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን ከልደተ ክርስቶስ እስከ 2000ዓ/ም** በተሰኘው የቤተክርስቲያኒቱ መጽሐፍ ላይ ዐቢይ ጾም ለምን እንደሚጾም ሲናገር፡- «ዐቢይ ጾም ወይንም ሁዳዴ ጌታ ከተጠመቀ በኃላ የጦመው አርባ ቀን ጦም ነው (ማቴ4፡-1)። ምዕመናን ጌታቸው ያደረገውን ተከትለው ይጦሙታል» ይላል (ገጽ 32 ላይ ይመልከቱ)። ጌታችንና መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ይህን ጾም የጾም ከፊቱ የተጋረጠበትን የዺያብሎስ ፈተና በድል ይወጣ ዘንድና አገልግሎቱን የሚጀምርበት ጊዜ በመሆኑ በመንፈስ ቅደስ ኃይል ይሞላ ዘንድ ነው፡- የሉቃስ ወንጌል 4፡-1፣2፣13፣14 «ኢየሱስም መንፈስ ቅዱስ መልቶበት ከዮርዳኖስ ተመለሰ፥ በመንፈስም ወደ ምድረ በዳ ተመርቶ፥ አርባ ቀን ከዲያብሎስ ተፈተነ። በነዚያም ቀኖች ምንም አልበላም፥ ከተጨረሱም በኋላ ተራበ። … ዲያብሎስም ፈተናውን ሁሉ ከጨረሰ በኋላ እስከ ጊዜው ከእርሱ ተለየ። ኢየሱስም በመንፈስ ኃይል ወደ ገሊላ ተመለሰ፤ ስለ እርሱም በዙሪያው ባለችው አገር ሁሉ ዝና ወጣ።»

       እንግዲህ ጌታችን ኢየሱስ ስለ ዳያቢሎስ ፈተናና ስለ መንፈስ ቅዱስ ኃይል መሞላት ጾም ጸሎትን ከያዘ እኛም ከእሱ የምንማረው ከዲያብሎስ ውጊያዎችና ፍላጻዎች እንሻገር ዘንድና ደግሞ በመንፈስ ቅዱስም ኃይል እንሞላ ዘንድ ጾሙን መጾም እንዳለብን ነው፡፡ በርግጥ ጌታችንና መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በመጀመርያ መሲሐዊ የአገልግሎት ዘመኑ የጾመውን የ40 ቀን ጾም፤ አስከትሎ በምድር ላይ በቀሩት ሁለቱ የአገልግሎት ዓመት ላይ በየዓመቱ ሲጾመው አላየንም፤ በተመሳሳይ መልኩም ደቀመዛሙርቱ ጌታችን የጾመው ጾም ነው ብለው ክርስቶስ ከአረገበትና በመንፈስ ቅዱስ ኃይል ከተሞሉ በኃላም ሲጾሙት፣ ደግሞም በትምህርት ደረጃም በየዓመቱ ልትጾሙት ይገባል ብለው ሲደነግጉ አላየንም። ነገር ግን በተለያየ ጊዜ በእግዚአብሔር ይፈታላቸው ዘንድ የያዙትን አጀንዳ በጾም በጸሎት ሲጠይቁ ማየት እንችላለን። ለምሳሌ፡- የሐዋርያት ሥራ 13፡- 1-2 «በአንጾኪያም ባለችው ቤተ ክርስቲያን ነቢያትና መምህራን ነበሩ፤ እነርሱም በርናባስ፥ ኔጌር የተባለው ስምዖንም፥ የቀሬናው ሉክዮስም፥ የአራተኛው ክፍል ገዥ የሄሮድስም ባለምዋል ምናሔ፥ ሳውልም ነበሩ። እነዚህም ጌታን ሲያመልኩና ሲጦሙ መንፈስ ቅዱስ። በርናባስንና ሳውልን ለጠራኋቸው ሥራ ለዩልኝ አለ።» በዚህ ክፍል በአንጾኪያ ባለችው ቤተክርስቲያን በጾም በጸሎትና በአምልኮ ተወስነው የተጉ ክርስቲያኖች ይኖሩ እንደነበርና በዚህም የመንፈስ አንድነት ውስጥ መንፈስ ቅዱስ ለአገልግሎቱ በርናባስንና ሳወልን ለዩልኝ ሲል እንመለከታለን። እንግዲህ ከደቀመዛሙርቱ እንደምንማረው ክርስቶስ ከተጋረጠበት ፈተና ዲያብሎስን ድል ይነሳ ዘንድ በመጾም እንዳስተማረን ሁሉ እንዲሁ በሚገጥሙን ፈተናዎችና ሁኔታዎች ከእግዚአብሄር ዘንድ መልስን እንድንቀበል መጾም መጸለይ እንዳለብን ነው።

      ታዲያ ግን አንዳንድ ኦርቶዶክሳውያን ጾም ማለት //ከጥሉላት// ወይንም ቅባት ካለባቸው ምግቦች መከልከል እንደሆነ አድርገው ያስባለሉ። በዚህም የተሳሳተ መረዳት ምክንያት የቤተክርስቲያናችን ምእመናን ጾመ ዐብይን የሚቀበሉት በመንፈስ ቅዱስ ምሪት ሳይሆን ሥጋና ቅቤ በመብላት ወይንም ደግሞ ድሃ ከሆኑ ቂጣ ላይ በተለቀለቀች አዋዜ ነው። ይህንም የጾም አቀባበል «ቅበላ» ይባላል፡፡ ለዚህም እንደማስረጃ አድርገው ንጉስ ዳዊትና ነብዩ ዳንኤልን ያቀርባሉ። ነገር ግን በመጽሀፍ ቅዱስ ውስጥ በጾም ወራት ላይ «ከመብል ሁሉ መከልከልን እንጂ ከስጋና ከቅቤ ለይቶ መከልከልን» አያስተምርም። ቤተክርስቲያናችን በዚሁ **የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን ከልደተ ክርስቶስ እስከ 2000ዓ/ም** በተሰኘው መጽሐፏ ላይ ስለ ጾም ስርዓት ባተተችበት ክፍል ላይ፡- «በማንኛውም የሐይማኖት ስርዓት ጾም አለ፤ የአፈጻጸም ስርዓቱ ግን የተለያየ ሆኖ ይታያል፤ ለምሳሌ ያህልም ዕብራውያን (እስራኤላውያን) ሲጾሙ ውለው ማታ ጥሉላት(ሥጋና ቅቤ) ይመገባሉ።» ይሄ ማለት በጾም ወራት ሥጋ ይመገቡ እንደነበር የሚያሳይ ነው፡፡ ንጉስ ዳዊትም ሆነ ዳንኤል ከምግቡ ሁሉ ማለትም ከሥጋ፣ ከቅቤ፣ ከማለፊያ እንጀራ ወዘተ ሲጾሙ ውለው ማታ ላይ የተገኘውን ምግብ ማለትም ሥጋም ይሁን ቅቤ እንደሚመገቡ ይነግረናል (ገጽ 31 ላይ ይመልከቱ)። እዚህ ላይ አንድ ጥያቄ መነሳቱ አይቀሬ ነው፡- እርሱም ‹‹ታዲያ ለምንድን ነው በጾም ወራት ከጥሉላት ወይንም ከሥጋና ከቅቤ ምግብ የምንከለከለው?››፡፡ ሁሉም ኦርቶዶክሳዊ ምዕመን ማወቅ ያለበት ጾምን ከጥሉላት ወይንም ከስጋና ቅቤ በመከልከል እንድጾም ቤተክርስቲያናችን የምታስተምረው //በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ ተመስራታ ሳይሆን እራሷ ባወጣችው ደንብና ስርዓት// ተነሳታ የምታስተምር መሆኑን በማወቅ ለሥጋ ምቾትን ከሚስጡ ከሥጋና ከቅቤ ምግቦች በመከልከል ይበልጥ ሥጋን በማዋረድና በማድከም በእግዚአብሔር ፊት በብዙ መቃተት እንቀርብ ዘንድ በማስብ የተመሰረት ቀናዒ-ሥርዓት መሆኑን ነው፡፡

      ከዚህ ከቤተክርስቲያናችን አስተምህሮ በመነሳት ሁሉም ኦርቶክሳዊ +ሁዳዴን+ ለጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ክብር በመስጠት መጾም ካለበት፡-

  1. ጾመ ዐቢይን የምንጾመው ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በመጾም ምሳሌን በመተዉ ምክንያት ተተርሰን ካሉብን ወቅታዊ ፈተናዎችና ተግዳሮቶች እንዲሁም ሐገራዊ ከሆነ አጀንዳዎች እንደ እግዚአብሄር ፈቃድ ልንጾምና በጸሎት ልንተጋ ያስፈልገናል።
  2. ጾመ ዐቢይን ለመቀበል ሥጋና ቅቤ እየተመገቡ ከመቀበል //ቅበላ// ከማድረግ ይልቅ በመንፈስ ቅዱስ ምሪት ‹‹ለሐገር፣ ለምዕመናን፣ ለዓለማችን፣ ለትውልዱ ሁሉ ያለውን የእግዚአብሔርን አጀንዳ በማስተዋል ነው ሁላችንም›› ጾሙን መቀበል ያለብን።
  3. በዚህ ጾም ወራት ከዓይንና ከሥጋ አምሮት፣ ከመጻና ከልዩ ልዩ ዓመጻዎች ሁሉ ተከልክሎ በንስሃና በመንፈስ ቅዱስ ሐሳብ ወደ እግዚአብሔር ለመቅረብ ነው ማተኮር ይገባናል።
  4. ጾሙ ከጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ጋር መያያዙ ካልቀረ **መሰበክ ያለበትም ጌታችንና መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ሊሆን ይገባዋልና፣ በዚህ የጾም ወራት የኢየሱስ ክርስቶስን ብቸኛ አዳኝነትና ሕይወትነት ቤተክርስቲያናችን አጥብቃ ምዕመናኗን ልታስተምር** ይገባል።
  5. ‹‹ጾም ያለ ጸሎት የምግብ ዐድማ›› መሆኑን ሁሉም ኦርቶዶክሳዊ በማስተዋል፣ በቅነንትና በታማኝነት ዕለት ዕለት በእግዚአብሔር ፊት በብዙ ጸሎት፣ በብዙ ንሥሃ በመውደቅ በመጾም ወደ አምላኩ ወደ እግዚአብሔር ሊቀርብ ይገባዋል፡፡

መልካም የጾም ጊዜ ይሁንል!