እናት ኦርቶዶክሳዊት ተዋህዶ ቤተክርስቲያናችን ካሏት አጽዋማት መካከል አንዱና ዋነኛው //ዐቢይ ጾም ወይንም ሁዳዴ// የሚባለው ነው። «ሁዳዴ» የሚለውን ቃል የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን ከልደተ ክርስቶስ እስከ 2000ዓ/ም በሚለው በሊቃነ ጳጳሳቱ የተጻፈው መጽሐፍ በገጽ 32 ላይ እንዲህ ሲል ይፈታዋል፡- «ዐቢይ ጾም መባሉም የጌታ ጾም ስለሆነ ነው፣ ታላላቅ የሰይጣን ፈተናዎች (አርእስተ ኃጣውእ) ድል የተነሱበት፣ ድል የሚነሱበት ስለሆነ ነው፣ በሕዝቡም ዘንድ ሁዳዴ ይባላል። ሁዳዴ ማለት የመንግስት መሬት የመንግስት ርስት ማለት ነው።» ይለናል።
በዚሁ **የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን ከልደተ ክርስቶስ እስከ 2000ዓ/ም** በተሰኘው የቤተክርስቲያኒቱ መጽሐፍ ላይ ዐቢይ ጾም ለምን እንደሚጾም ሲናገር፡- «ዐቢይ ጾም ወይንም ሁዳዴ ጌታ ከተጠመቀ በኃላ የጦመው አርባ ቀን ጦም ነው (ማቴ4፡-1)። ምዕመናን ጌታቸው ያደረገውን ተከትለው ይጦሙታል» ይላል (ገጽ 32 ላይ ይመልከቱ)። ጌታችንና መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ይህን ጾም የጾም ከፊቱ የተጋረጠበትን የዺያብሎስ ፈተና በድል ይወጣ ዘንድና አገልግሎቱን የሚጀምርበት ጊዜ በመሆኑ በመንፈስ ቅደስ ኃይል ይሞላ ዘንድ ነው፡- የሉቃስ ወንጌል 4፡-1፣2፣13፣14 «ኢየሱስም መንፈስ ቅዱስ መልቶበት ከዮርዳኖስ ተመለሰ፥ በመንፈስም ወደ ምድረ በዳ ተመርቶ፥ አርባ ቀን ከዲያብሎስ ተፈተነ። በነዚያም ቀኖች ምንም አልበላም፥ ከተጨረሱም በኋላ ተራበ። … ዲያብሎስም ፈተናውን ሁሉ ከጨረሰ በኋላ እስከ ጊዜው ከእርሱ ተለየ። ኢየሱስም በመንፈስ ኃይል ወደ ገሊላ ተመለሰ፤ ስለ እርሱም በዙሪያው ባለችው አገር ሁሉ ዝና ወጣ።»
እንግዲህ ጌታችን ኢየሱስ ስለ ዳያቢሎስ ፈተናና ስለ መንፈስ ቅዱስ ኃይል መሞላት ጾም ጸሎትን ከያዘ እኛም ከእሱ የምንማረው ከዲያብሎስ ውጊያዎችና ፍላጻዎች እንሻገር ዘንድና ደግሞ በመንፈስ ቅዱስም ኃይል እንሞላ ዘንድ ጾሙን መጾም እንዳለብን ነው፡፡ በርግጥ ጌታችንና መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በመጀመርያ መሲሐዊ የአገልግሎት ዘመኑ የጾመውን የ40 ቀን ጾም፤ አስከትሎ በምድር ላይ በቀሩት ሁለቱ የአገልግሎት ዓመት ላይ በየዓመቱ ሲጾመው አላየንም፤ በተመሳሳይ መልኩም ደቀመዛሙርቱ ጌታችን የጾመው ጾም ነው ብለው ክርስቶስ ከአረገበትና በመንፈስ ቅዱስ ኃይል ከተሞሉ በኃላም ሲጾሙት፣ ደግሞም በትምህርት ደረጃም በየዓመቱ ልትጾሙት ይገባል ብለው ሲደነግጉ አላየንም። ነገር ግን በተለያየ ጊዜ በእግዚአብሔር ይፈታላቸው ዘንድ የያዙትን አጀንዳ በጾም በጸሎት ሲጠይቁ ማየት እንችላለን። ለምሳሌ፡- የሐዋርያት ሥራ 13፡- 1-2 «በአንጾኪያም ባለችው ቤተ ክርስቲያን ነቢያትና መምህራን ነበሩ፤ እነርሱም በርናባስ፥ ኔጌር የተባለው ስምዖንም፥ የቀሬናው ሉክዮስም፥ የአራተኛው ክፍል ገዥ የሄሮድስም ባለምዋል ምናሔ፥ ሳውልም ነበሩ። እነዚህም ጌታን ሲያመልኩና ሲጦሙ መንፈስ ቅዱስ። በርናባስንና ሳውልን ለጠራኋቸው ሥራ ለዩልኝ አለ።» በዚህ ክፍል በአንጾኪያ ባለችው ቤተክርስቲያን በጾም በጸሎትና በአምልኮ ተወስነው የተጉ ክርስቲያኖች ይኖሩ እንደነበርና በዚህም የመንፈስ አንድነት ውስጥ መንፈስ ቅዱስ ለአገልግሎቱ በርናባስንና ሳወልን ለዩልኝ ሲል እንመለከታለን። እንግዲህ ከደቀመዛሙርቱ እንደምንማረው ክርስቶስ ከተጋረጠበት ፈተና ዲያብሎስን ድል ይነሳ ዘንድ በመጾም እንዳስተማረን ሁሉ እንዲሁ በሚገጥሙን ፈተናዎችና ሁኔታዎች ከእግዚአብሄር ዘንድ መልስን እንድንቀበል መጾም መጸለይ እንዳለብን ነው።
ታዲያ ግን አንዳንድ ኦርቶዶክሳውያን ጾም ማለት //ከጥሉላት// ወይንም ቅባት ካለባቸው ምግቦች መከልከል እንደሆነ አድርገው ያስባለሉ። በዚህም የተሳሳተ መረዳት ምክንያት የቤተክርስቲያናችን ምእመናን ጾመ ዐብይን የሚቀበሉት በመንፈስ ቅዱስ ምሪት ሳይሆን ሥጋና ቅቤ በመብላት ወይንም ደግሞ ድሃ ከሆኑ ቂጣ ላይ በተለቀለቀች አዋዜ ነው። ይህንም የጾም አቀባበል «ቅበላ» ይባላል፡፡ ለዚህም እንደማስረጃ አድርገው ንጉስ ዳዊትና ነብዩ ዳንኤልን ያቀርባሉ። ነገር ግን በመጽሀፍ ቅዱስ ውስጥ በጾም ወራት ላይ «ከመብል ሁሉ መከልከልን እንጂ ከስጋና ከቅቤ ለይቶ መከልከልን» አያስተምርም። ቤተክርስቲያናችን በዚሁ **የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን ከልደተ ክርስቶስ እስከ 2000ዓ/ም** በተሰኘው መጽሐፏ ላይ ስለ ጾም ስርዓት ባተተችበት ክፍል ላይ፡- «በማንኛውም የሐይማኖት ስርዓት ጾም አለ፤ የአፈጻጸም ስርዓቱ ግን የተለያየ ሆኖ ይታያል፤ ለምሳሌ ያህልም ዕብራውያን (እስራኤላውያን) ሲጾሙ ውለው ማታ ጥሉላት(ሥጋና ቅቤ) ይመገባሉ።» ይሄ ማለት በጾም ወራት ሥጋ ይመገቡ እንደነበር የሚያሳይ ነው፡፡ ንጉስ ዳዊትም ሆነ ዳንኤል ከምግቡ ሁሉ ማለትም ከሥጋ፣ ከቅቤ፣ ከማለፊያ እንጀራ ወዘተ ሲጾሙ ውለው ማታ ላይ የተገኘውን ምግብ ማለትም ሥጋም ይሁን ቅቤ እንደሚመገቡ ይነግረናል (ገጽ 31 ላይ ይመልከቱ)። እዚህ ላይ አንድ ጥያቄ መነሳቱ አይቀሬ ነው፡- እርሱም ‹‹ታዲያ ለምንድን ነው በጾም ወራት ከጥሉላት ወይንም ከሥጋና ከቅቤ ምግብ የምንከለከለው?››፡፡ ሁሉም ኦርቶዶክሳዊ ምዕመን ማወቅ ያለበት ጾምን ከጥሉላት ወይንም ከስጋና ቅቤ በመከልከል እንድጾም ቤተክርስቲያናችን የምታስተምረው //በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ ተመስራታ ሳይሆን እራሷ ባወጣችው ደንብና ስርዓት// ተነሳታ የምታስተምር መሆኑን በማወቅ ለሥጋ ምቾትን ከሚስጡ ከሥጋና ከቅቤ ምግቦች በመከልከል ይበልጥ ሥጋን በማዋረድና በማድከም በእግዚአብሔር ፊት በብዙ መቃተት እንቀርብ ዘንድ በማስብ የተመሰረት ቀናዒ-ሥርዓት መሆኑን ነው፡፡
ከዚህ ከቤተክርስቲያናችን አስተምህሮ በመነሳት ሁሉም ኦርቶክሳዊ +ሁዳዴን+ ለጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ክብር በመስጠት መጾም ካለበት፡-
- ጾመ ዐቢይን የምንጾመው ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በመጾም ምሳሌን በመተዉ ምክንያት ተተርሰን ካሉብን ወቅታዊ ፈተናዎችና ተግዳሮቶች እንዲሁም ሐገራዊ ከሆነ አጀንዳዎች እንደ እግዚአብሄር ፈቃድ ልንጾምና በጸሎት ልንተጋ ያስፈልገናል።
- ጾመ ዐቢይን ለመቀበል ሥጋና ቅቤ እየተመገቡ ከመቀበል //ቅበላ// ከማድረግ ይልቅ በመንፈስ ቅዱስ ምሪት ‹‹ለሐገር፣ ለምዕመናን፣ ለዓለማችን፣ ለትውልዱ ሁሉ ያለውን የእግዚአብሔርን አጀንዳ በማስተዋል ነው ሁላችንም›› ጾሙን መቀበል ያለብን።
- በዚህ ጾም ወራት ከዓይንና ከሥጋ አምሮት፣ ከመጻና ከልዩ ልዩ ዓመጻዎች ሁሉ ተከልክሎ በንስሃና በመንፈስ ቅዱስ ሐሳብ ወደ እግዚአብሔር ለመቅረብ ነው ማተኮር ይገባናል።
- ጾሙ ከጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ጋር መያያዙ ካልቀረ **መሰበክ ያለበትም ጌታችንና መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ሊሆን ይገባዋልና፣ በዚህ የጾም ወራት የኢየሱስ ክርስቶስን ብቸኛ አዳኝነትና ሕይወትነት ቤተክርስቲያናችን አጥብቃ ምዕመናኗን ልታስተምር** ይገባል።
- ‹‹ጾም ያለ ጸሎት የምግብ ዐድማ›› መሆኑን ሁሉም ኦርቶዶክሳዊ በማስተዋል፣ በቅነንትና በታማኝነት ዕለት ዕለት በእግዚአብሔር ፊት በብዙ ጸሎት፣ በብዙ ንሥሃ በመውደቅ በመጾም ወደ አምላኩ ወደ እግዚአብሔር ሊቀርብ ይገባዋል፡፡
መልካም የጾም ጊዜ ይሁንል!
No comments:
Post a Comment