ክፍል ሁለት
በዲያቆን ይስማዕከ ይነግስ
እናት ኦርቶዶክሳዊት ተዋህዶ ቤተክርስቲያናችን
ከመሰረቷ አንስታ እስከ
ጉልላቷ፥ ክብሯና ማዕረጓ፥ የማምለጫ አለቷ፥ የጌቶቹ ሁሉ ጌታ መድኃኒታችን ኢየሱስ
ክርስቶስ ነው፡፡ በመልካሙ አዝማራ መሐል እንክርዳድ
አይጠፋምና አንዳንድ ለሆዳቸው ያደሩ እኩያነ መናፍቃን እንግዳ አስተምህሮ በቤተክርስቲያናችን ውስጥ ሲያስተምሩ ይደመጣል፡፡ ለስህተት
ትምህርታቸው ዐውደ ምንባቡንና ጥቅል የቃለ እግዚአብሔርን አስተምህሮ ማዕከል ሳያደርጉ እንዲሁ ቃል ይጠቅሳሉ፥
·
“ሰው እናታችን ጽዮን ይላል፥ በውስጥዋም ሰው ተወለደ እርሱ ራሱም ልዑል መሠረታት።
እግዚአብሔር ለሕዝቡ፥ በውስጥዋም ለተወለዱት አለቆችዋ በመጽሐፍ ይነግራቸዋል። በአንቺ የሚኖሩ ሁሉ ደስ እንደሚላቸው ይነግራቸዋል።” መዝ 86(87)፥5-7፡፡
·
በዚህ ክፍል “እናታችን ጽዮን” የተባለችው ቅድስት ድንግል ማርያም ናት በማለት ይናገራሉ፡፡
እኛም በበኩላች ቅድስት ቤተክርስቲያን እንዳስተማረችን እንዲህ እንላለን፡-
1. በመጀመርያ ይህን የምስጋና መዝሙር የተቀኙት የቆሬ ልጆች እንጂ ዳዊት አይደለም (የምዕራፉን ርዕስ ይመልከቱ)፡፡ ሲቀጥል
ቁጥር 1 ላይ “መሠረቶቹ በተቀደሱ ተራሮች ናቸው” እንደሚል ዝማሬው፥ በወንድ አንቀጽ ሲጠራ እንጂ “መሰረቶቿ” የሚል ቃልን አናነብም፡፡
አንዳንድ ግለሰቦች በስብከታቸውና በመጽሐፋቸው ላይ ሲዘግቡ ግን “መሰረቶቿ በተቀደሱ ተራሮች ነው” በማለት ለድንግል ማርያም አላግባብ በመቀጸል ለሚለፉት ልፈፋ ተሐቅቦ ይሆንላቸው ዘንድ እንደቃሉ እንመክራለን፡፡
2. አስቀጥሎም በዝማሬው ቁጥር ከ2-3 ላይ “ከያዕቆብ ድንኳኖች ይልቅ፥ እግዚአብሔር የጽዮንን ደጆች ይወድዳቸዋል። የእግዚአብሔር ከተማ ሆይ፥ በአንቺ የተከበረ ነገር ይባላል።” እንደሚል ዝማሬው “የጽዮን ደጆች” ብዛት ያላቸው መሆናቸው ስለሚነግረን ድንግል ማርያም
ናት ማለት ክህደት ይሆናል፡፡ ብዛት ያለው ደጅ የሚገባው ለሐገር አልያም ለከተማ እንጂ ለተወደደችው ለቅድስት ድንግል ማርያም አይደለም፡፡
ድንግል ማርያም ብዙ ደጆች አሏት ብሎ ባለማስተዋልም ቢሆን እንደ
ማህበረ ቅዱሳን መስበክ፥ ስድብ ካልሆነ በቀር እውነታነት የለውም፡፡ ለዛም ነው፥ የእግዚአብሔር ከተማ በመባል
ብዛት ባለው ደጆች የተገለጠችው፡፡ ይህችው የእግዚአብሔር ከተማ፥ በክፍሉ እንደምንመለከተው “ጽዮን” በሚል ስያሜ ነው
የተጠራችው፡፡ ዐውደ ምንባቡ የእግዚአብሔር ከተማ ስለተባለችው ጽዮን እንጂ ስለ ድንግል ማርያም የሚያወራ አይደለም
የሚያስጠርጥርም ነገር አይናገርም፡፡
3. ቁጥር 5 እንዲህ ይነበባል፡- “ሰው እናታችን ጽዮን ይላል፥ በውስጥዋም ሰው ተወለደ እርሱ ራሱም ልዑል መሠረታት፡፡” በዚህ ዝማሬ ላይ የእግዚአብሔር
ከተማ የተባለችው፣ ብዛት ያለው ልጆች ያሏት የጽዮን ከተማ፣ በውስጧ ሰው እንደተወለደ፣ ከዚህም የተነሳ “እናት” ልትባል እንደቻለች
ይነግረናል፡፡ በዚህ ምንባብ ሁሉም ሰው ሊያስተውል የሚገባው “በውስጥዋም ሰው ተወለደ” እንጂ “ከእርሷም ሰው ተወለደ” ተብሎ አለመጻፉን ይሆናል፡፡ ይህም የሚያሳየን ከተማይቱ
ጽዮን “በውስጧ ሰው ተወለደ” የተባለችው ሐገር በመሆኗ እንደሆነ የተገለጠ ነው፡፡ ከዚህ በተረፈ እንደ ደባትራኑ የበሬ ወለደ ቅዠት ካለፈፍን በቀር
“በሰው ማህጸን ውስጥ ሰው ሊጸነስ እንጂ ሊወለድ ከቶ እንደማይችል” በሁሉ ዘንድ የታወቀ ነው፡፡ “በሰው ውስጥ ሰው ተወለደ” ብሎ መስበክ 21ኛው ክፍለ ዘመንን የማይመጥን ተራ ተረት ይሆንብናል፡፡
4. በተጨማሪም በዚህ ክፍል “ሰው እናታችን ጽዮን ይላል” እንደሚል ቃሉ “እናታችን” እንጂ “እናቱ” አለማለቱን ልብ
ይሏል፡፡ ይህም የሚያሳየን በጽዮን ከተማ ውስጥ የተወለዱት ሰዎች ብዛት ያለቸው በመሆናቸው ምክንያት //እናታችን// እያሉ ሊጠሯት
መቻላቸውን ነው፡፡ ከዚህ በተለየ ሁኔታ ግን ጽዮን የተባለችው የእግዚአብሔር ከተማ አንድ ልጅ ብቻ መውለዷን ዝማሬው አያስተምረንም፡፡
5. ይቀጥልና ቁጥር 6 ላይ በተመሳሳይ መልኩ “በውስጥዋም ለተወለዱት አለቆችዋ በመጽሐፍ ይነግራቸዋል።” በማለት ከጽዮን የተወለዱት በቁጥር ያልተገለጡ ነገር ግን ብዙ ሰዎች መሆናቸው ይነግረናል፡፡ ብዛት ያላቸው የጽዮን
ልጆች እናታችን
እያሉ እንደሚጠሯት እንጂ ጽዮን አንድ ልጅ ብቻ ስለመውለዷ ክፍሉ አይናገርም፡፡ እነዚህ ብዛት ያላቸው የጽዮን ልጆች “በውስጥዋም ለተወለዱት አለቆችዋ ” እንደሚል ቃሉ መልሰው በራሷ በጽዮን ላይ “አለቆች” እንደሆኑ ይነግረናል፡፡ እንግዲህ ይህን ግልጽ የዝማሬ
መልዕክት በምን በኩል ቢሰላ ነው ለድንግል ማርያም ልንቀጽለው የሚገባን? እንዲሁ ድንግል ማርያምን ከፍ ያደረግናት እየመሰለን፥
መንፈስ ቅዱስ የማይከብርበትን የሰዎች ፍልስፍና በማስተጋባት፥ ቃሉ የማያስተምረውን በመንዛት፥ በማወቅም ይሁን ባለማወቅ ድንግልን
እያጥላላን መሆኑን ልብ ልንል ይገባል፡፡
6. በዝማሬው የመጨረሻ ቁጥር እንዲህ ተብሎ ተደምድሟል፡- “በአንቺ የሚኖሩ ሁሉ ደስ እንደሚላቸው ይነግራቸዋል።” በማለት ጽዮን
የሰዎች መኗሪያ ከተማ እንደሆነች በግላጭ ያስረዳናል፡፡ ጽዮን የመኖሪያ ከተማ ከመሆኗም ባሻገር በአንቺ “የሚኖሩ” በማለት በጽዮን ውስጥ የሚኖሩ እጅግ በርካታ ሰዎች መሆናቸውን ይነግረናል፡፡ ከዚህ በተረፈ ድንግል ማርያም ክርስቶስን ለ 9 ወር
በማህጸኗ እንደተሸከመች እንጂ በማህጸኗ ውስጥ ክርስቶስ መኗሪያውን አበጅቶ እንደነበር ሁሉ ቤተክርስቲያን አላስተማረችንም፡፡
እንግዲህ ቃሉንና ቤተክርስቲያንን እናድምጥ ወይስ የደብተራዎችን ቅዠት እናድምጥ?
... ይቀጥላል ...
ግሩም ግሩም ግሩም!! በጨለማ ብርሃን ይብራ ያለ እግዚአብሔር ነውና በኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን ስለተነሳው የእግዚአብሔር ሠራዊት ስሙን እባርካለሁ፡፡ ኢየሱስ ጌታ ነው!!
ReplyDeleteብዛት ያለው ደጅ የሚገባው ለሐገር አልያም ለከተማ እንጂ ለተወደደችው ለቅድስት ድንግል ማርያም አይደለም፡፡ ድንግል ማርያም ብዙ ደጆች አሏት ብሎ ባለማስተዋልም ቢሆን እንደ ማህበረ ቅዱሳን መስበክ፥ ስድብ ካልሆነ በቀር እውነታነት የለውም፡፡ ለዛም ነው፥ የእግዚአብሔር ከተማ በመባል ብዛት ባለው ደጆች የተገለጠችው፡፡
ReplyDelete