እንኳን ለሆሣዕና በዓል
አደረሰን! አደረሳችሁ!
“ሆሣዕና” የሚለው ቃል ከአሮማይክ ሁለት ቃላት የተጣመረ ሲሆን ትርጓሜውም “አሁን አድን” የሚል
ነው፡፡ የዕብራይስጡ “ሆሻአና” የሚለው ቃል ከአሮማይኩ ቃል የተገኘ ሲሆን፥ ጥንታዊ የቅዱሳት መጻሕፍት ጥናት ”הֹושִׁ֘יעָ֥ה, 3467 hō-wō-šî-‘āh
ሆሻአና” በማለት ያስቀምጠዋል፡፡ ይህንኑ ቃል በመዝሙር መጽሐፍ ቅዱስ ዳዊት አስቀድሞ
በትንቢት መንፈስ “ሆሣዕና” በማለት ጌታችን ኢየሱስ
ማዳኑን እንዲያፈጥን ሲማጸነው እንመለከታለን፥
·
“አቤቱ፥ እባክህ፥ አሁን አድን አቤቱ፥ እባክህ፥ አሁን አቅና፡፡ Save
now, I beseech thee, O Lord: O Lord, I beseech thee, send now prosperity. אָנָּ֣א יְ֭הוָה הֹושִׁ֘יעָ֥ה נָּ֑א אָֽנָּ֥א יְ֝הוָ֗ה הַצְלִ֘יחָ֥ה נָּֽא׃” መዝ ፻፲፰፥፳፭ ፡፡ (በነገራችን
ላይ በዚህ ክፍል ንጉስ ዳዊት “ያህዌ יְ֭הוָה, Yah-weh” በማለት ሲማጽን የምንመለከተው ጌታችን ኢየሱስን
ነው፡፡ ይህም ጌታችን ኢየሱስ ሁሉን ቻይ አምላክ፣ ያለና የነበረ ደግሞም የሚኖር፣ ያህዌ መሆኑን የሚያስረዳ ነው፡፡)
አባቶች በመንፈስ ቅዱስ ምሪት አዳኝ ስለሆነው
መሲህ በቅዱሳት መጻሕፍት ዘገባ መሰረት፥ አብዝተው ትንቢትን የተናገሩለት ሲሆን ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ያድናቸው ዘንድ፥ በውርጭላ
ላይ ተቀምጦ ከደብረ ዘይተና ከቤተ ፋጌ ወደ ቤተልሔም እንደሚመጣ፥ ነብዩ ዘካርያ በትንቢት መጽሐፉ ላይ እንዲህ ሲል አስፍሯል፥
·
“አንቺ የጽዮን ልጅ ሆይ፥ እጅግ ደስ ይበልሽ አንቺ የኢየሩሳሌም ልጅ ሆይ፥ እልል
በዪ እነሆ፥ ንጉሥሽ ጻድቅና አዳኝ ነው ትሑትም ሆኖ በአህያም፥ በአህያይቱ ግልገል በውርጫይቱ ላይ ተቀምጦ ወደ አንቺ ይመጣል” ዘካ ፱፥፱፡፡
ጌታችን
ኢየሱስ ክርስቶስም አባቶች በትንቢት እንደተናገሩለት፥ የዘመኑ ፍጻሜ፥ ሰዓቱ በደረሰ ጊዜ፥ “እባክህ አሁን አድን”
እያሉ የለመኑትን ቃል ሰምቶ፥ ከቅድስት ድንግል ማርያም ያለዘርዓ ብእሲ ሥጋ ሆኖ በመወለድ፥ የዓለምን ኃጢአት በስጋው ተሸክሞ ወደ
እግዚአብሔር መንግስት አፍልሶናል፡፡ በመጽሐፍ እንደተነገረለት በአህያይቱ ውርጭላ ላይ ጌታችን ተቀምጦ ወደ ቤተልሔም በገባ ጊዜ
ከሕጻን እስከ አዛውንቱ ድረስ ልብሳቸውንም አንጥፈው ተቀበለውታል፥ የዘንባባ ዝንጣፊውንም በእጃቸው ጨብጠው ለክብሩ ተቀኝተውለታል፥
እንዲህም እያሉ በአንድነት ይዘምሩለት ነበር፥
·
“የሚቀድሙትም ሕዝብ የሚከተሉትም። ሆሣዕና ለዳዊት ልጅ በጌታ ስም የሚመጣ የተባረከ
ነው፤ ሆሣዕና በአርያም እያሉ ይጮኹ ነበር” ማቴ ፳፩፥፱፡፡ አሜን! አሜን! ሆሣዕና በአርያም! ለዳዊት ልጅ ለጌታችን ኢየሱስ!
ሃሌሉያ!
የሚገርመው ግን የካህናት አለቆች፥ በመጻሕፍት
የተነገሩት በሙሉ እየተፈጸሙ መሆኑን ተመልክተው፥ ልባቸውን ወደ እግዚአብሔር ልጅ፥ ወደ እውነተኛው መሲሕ፥ ወደ ጌታችን ኢየሱስ
ክርስቶስ ከማዘንበል ይልቅ ክፍትን በልባቸው ተሞልተው ይቃወሙት ነበር፡፡ ዛሬስ ስንቶቻችን እንሆን “ስለ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በተሰበከ ጊዜ፥ ቅዱስ ስሙ በዝማሬ በተመሰገነ ጊዜ ልባችን የሚከፋው? ስንቱንስ ከእናት
ቤተ ክርስቲያን መናፍቅ፥ ጴንጤ እያልን ገፍተን አባረርነው?” በእውነት፥ ምህረትና ቸርነቱ ይብዛልን! አይሁድ
ጌታችንን ከማክበር ይልቅ ልባቸውን በሐሰት ክስ ሞልተው፥ የሠራቸውን ተአምራት ተመልክተው፥ ሕዝቡም ሁሉ በዝማሬ ሲያመሰግኑት አይተው፥
ይገዳደሩት ዘንድ በቅንዓት ተነሱበት እንዲህ ሲሉ፥
·
«ነገር ግን የካህናት አለቆችና ጻፎች ያደረገውን ድንቃ ድንቅ በመቅደስም፣ ሆሣዕና ለዳዊት ልጅ እያሉ
የሚጮኹትን ልጆች ባዩ ጊዜ፥ ተቈጥተው፣ እነዚህ የሚሉትን አትሰማምን? አሉት» ማቴ ፳፩፣ ፲፭፡፡
ጌታችንና መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስም “እውነት
ብላችኋል፥ ለእኔ ዝማሬ አይገባም” አላላቸውም፥ ይልቁንም የቅዱሳት መጻሕፍትን የትንቢት ቃል ነበር ማስረጃ አድርጎ በማቅረብ (“ከሕፃናትና ከሚጠቡ ልጆች አፍ ምስጋናን አዘጋጀህ” መዝ ፰፥፪) ምስጋና የተገባው እውነተኛ ጌታና አምላክ መሆኑን
እንዲህ ሲል ነበር ያረጋገጠላቸው፥
·
«እሰማለሁ፤ ከሕፃናትና ከሚጠቡት አፍ ምስጋናን ለራስህ አዘጋጀህ የሚለውን ቃል ከቶ አላነበባችሁምን?
አላቸው» ማቴ ፳፩፥፲፮፡፡
በእውነት ጌታችን ኢየሱስ አድኖናል፥ ቤዛ ሆኖ ነፍሳንን ከዘለዓለም ሞት አድኗታል፥ በትንቢት እንደተነገረለት ሕዝቡን
ሁሉ ከኃጢአት ለማዳን ሲል ራሱን መስዋዕት አድርጎል፥ ይኽውም እስከ መስቀል ሞት የታመነ ሆኗል፥ ስለ እኛም በደል ርግማን ሆኖ
ከሕግ ርግምን ዋጅቶናል፥ እንደሞተም አልቀረም በክብር ሞትን ድል ነስቷል፥ በኃይልና በልዕልና ወደ ሰማያት ከፍታ በማረግ በአባቱ
ቀኝ በክብር ተቀምጧል፡፡ ደግሞም ወደ አባቱ ሊወስድን ተመልሶ ይመጣል! ክብር ይግባው!!
አሜን! ሆሣዕና በአርያም! ለዳዊት ልጅ ለጌታችን ኢየሱስ! ሃሌሉያ!
ግርም የምትለኝ አህያይቱ ናት ፡፡ ጌታዋ እርሱ ከፈቀደላት ክልል እንዳትርቅ አድርጎ ያለ አገልግሎት እስሮ አስቀምጧት የነበረች “ማንም ያልተቀመጠባት” አህያ፡፡) የት እንዳለች፡፡ በምን ሁኔታ እንዳለች፡፡ ከጌታ በቀር ደቀመዛሙርቱም እንኳ ያላወቁላት አህያ፡፡ ስለ እርሷ ከጌታ አፍ ቃል ወጥቶአልና ቃሉን የተቀበሉ ደቀመዛሙርት አሁን ተንቀሳቀሱ ፡፡ ወደ አህያይቱ ፡፡ ጌታዋ ከከለለላት ክልል እንዳትወጣ አስሯት ባቆየበት ገመድ ታስራ ወዳለችው አህያ፡፡ በቃሉ ስልጣን “ማንም ቢጠይቃችሁ ለጌታ ታስፈልገዋለች በሉት” ብሎ ከቀድሞ ጌታዋና ከዚያ እስራቷም የፈታትንና “አምጡልኝ “ ብሎ የጠራትን ጌታ ልትሸከም እንድትችል ተፈታች አህያ፡፡ ትደንቃለች፡፡
ReplyDeleteአሁን ደግሞ ትክክለኛው ጌታዋ ጌታ ኢሱስ ክርስቶስ ተቀምጦባታልና!! ካሁን ቀደም የት ስለመሆኗ ያላወቁት ደቀመዛሙርት ሳይቀሩ ከተሸከመችው ጌታ የተነሳ ልብሳቸውን በእግሮቿ ስር ያነጠፉላትና ያጀቡዋት አህያ ፡፡ አሁን ከብበዋት “ሆሳዕና” እየተባለ ነው፡፡ “በጌታ ስም የሚመጣ የተባረከ ነው፡፡” እየተባለ ነው ፡፡ በማንም ስም ሳይሆን “በጌታ ስም የሚመጣ”….. ነው እያሉ ያሉት፡፡ “ብዙ ጌቶች” አሉና፤ “ብዙ ሃይማኖቶች”ም አሉና በነኝህ ጌቶቻቸውና የሃይማኖታቸው ፍቃድ ልክ በወሰኑላቸው ክልል ውስጥ ብቻ እንዲንቀሳቀሱና ወደ ጌታ ኢየሱስ እንዳይሄዱ ገደብ ተበጂቶባቸው ከታሰሩበት የእስራት ገመድ ተፈትተው ወደ እውነተኛው ጌታ፤ ወደ ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ ይመጡ ዘንድ ዛሬም ከራሱ አፍ የወጣ ቃል አለ፡፡ ያን ቃል ሰምተው የታሰሩትን ለመፍታት ደቀመዛሙርቱ ሂዱ ተብለዋላ፡፡
ተጠሪዎቹ “አህዮች” የተጠሩት ከቀደሙ ጌቶቻቸው ያልተለየ ወደሆነ ወደ ሌላ ጌታ አይደለም፡፡ የተጠሩት ወደ ሌላ ሓይማኖትም አይደለም፡፡ “እኔ ህይወት ነኝ፡፡” ብሎ “ሕይወት እንዲሆንላችሁ እንዲበዛላችሁም…. “ ወዳለው እውነተኛ ጌታ ነው፡፡ ጥሪው በቀጥታ “ህይወትን” የመለውጥ ብቃት ወዳለው ወደ ህይወት ወደ ራሱ ነው፡፡ ከማያምኑት ባልተለየ የሕይወት መልክ ላሉ ይህ የምስራች ነው፡፡ “ይሳኮር አጥንተ ብርቱ አህያ ነው፡፡ …ትካሻውን ለሸክም ዝቅ አደረገ ፡፡” ተብሎ እንደተጻፈውና እንደ ተፈታችው እንደዚያች አህያ ዛሬም የሚፈቱና ትከሻቸውን ለጌታ ዝቅ የሚያደርጉ አሉ፡፡ እኒህ “አህዮች” እንደዚያችኛይቱ አህያና እንደ ይሳኮርም ትከሻቸውን “ለሸክም ዝቅ” ቢያደርጉና ጌታን ለመሸከምም ቢፈቅዱ የሚሸከሙት ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ ይዞአቸው የሚሄደው “በጌታ ስም የሚመጣ የተባረከ ነው ፡፡ እያሉ የዘንባባ ዝንጣፊንና ልብሶቻቸውን በእግሮቻቸው ስር ወደ ሚያነጥፉላቸው ደቀመዛሙርቱና ተከታዮቹ ነው፡፡
ወገኔ!!! “ሃይማኖት” እንጂ “ህይወት” ከሌለዎት “ህይወት ይሻልሃል፡፡” ይላልና ቃሉ “ይህቺ ቀን” “ይህቺ ሰዓት” አትለፍዎት!! ሆሳዕናው ለእርስዎ ይሁንልዎት፡፡ የእስከዛሬው መውጣት መግባትዎ “በሌላ በማንም ስም” ሆኖ ቢሆን ይህ “የታሰሩበት ገመድ”ና አስራትዎ ራሱ ዛሬ በዚህ ቃል ይፈታል፡፡ የኔ ሳይሆን ከጌታ ከራሱ አፍ ወጣ ቃል ነውና በጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ ስም “ሁሉን” ወደ ሚያደርጉበት የህይወት ከፍታ ይመጣሉ ፡፡ በመጡበት በዚያም፤ “በጌታ ስም የሚመጣ የተባረከ ይሁን ፡፡” እያሉ እርስዎኑ ጭምር ሲባርኩዎትም ይሰማሉ፡፡ ከእርስዎ የሚፈለገው እንደ አህያቱ ጌታ ኢሱስ ክርስቶስን ለመሸከም ትከሻዎን (ፈቃድዎን ) ዝቅ ማድረግ ብቻ!! ለጌታ ያስፈልጉታልና!! ወደ ጌታ ይነሱ፡፡ ጌታ ከዚህ ጉዞው ለጥቆ ደግሞ ወደ ፍሬ አልባይቱ በለስ (እስራኤል / ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስን እምቢ ብላ ፍሬ አልባ ወደ ሆነችው ሃይማኖትም ) መጥቶ በጌታ በራሱ የምትረገምበትንና የምትደርቅበትን ክፍልም ልብ ይበሉት፡፡